July 4, 2024

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራ ነው – የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራ ነው – የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

የሀገሪቱን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶች በራስ አቅም መፍታት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መገባቱን የፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ሀገር በቀል ድጋፍን ማጠናከር በሚያስችሉ ጉዳዮችና ተሞክሮዎች ላይ ያተኮረ መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል።

የፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በሀገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት መመለስ የሚያስችል የአደጋ ስጋት አመራር ፖሊሲ ባሳለፍነው የካቲት ወር በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን አስታውሰዋል።

ፖሊሲው በዋናነት የሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎቶችን በራስ አቅም በመፍታት የተረጂዎችን ቁጥር መቀነስና በምግብና ስነ-ምግብ እጥረት የሚያጋጥመውን ችገር መፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።

የተረጂዎችን ቁጥር በመቀነስ ሂደትም የመረዳዳት ባህልንና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚ ሲሆን በተለይም በምግብና ስነ-ምግብ እጥረት ተጎጂ የሆኑ ህጻናትና እናቶችን ትኩረት ያደረገ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትና ከአራት ሚሊዮን የሚበልጡ የማህበረሰብ ክፍሎች በምግብና ስነ-ምግብ እጥረት ጉድለት ምክንያት ለተለያዩ ችግሮች ይጋለጣሉ ብለዋል።

በመሆኑም በየአካባቢው ባሉ ሀገር በቀል የሰብአዊ ድጋፍ ልምዶችና ተሞክሮዎችን በማስፋትና በማጠናከር የተረጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በምግብና ስነ-ምግብ ላይ የሚሰራው ስራ በአካልና በአዕምሮ የዳበሩ ህጻናትን በመፍጠር በትውልድ ግንባታ ላይ የሚያበረክተው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ እያንዳንዱ ቤተሰብ ለዚህ ከፍተኛ ድርሻ አለው ብለዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ቤተሰብ ለተረጂነት ሲጋለጥና ችግር ላይ ሲወድቅ የረጂ ድርጅቶችን ከመጠበቅ ይልቅ በቆየ ኢትዮጵያዊ ልምድ በአካባቢና ቀበሌ ደረጃ የመረዳዳት ባህልን ማሳደግ እንደሚገባ አንስተዋል።

ኮሚሽኑ በየአካባቢው ያሉ የመደጋገፍ ልምዶችን በተደራጀ መንገድ መምራት የሚያስችል እቅድ ነድፎ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን የመድረኩ ትኩረትም በሀገር በቀል ድጋፎች በመታገዝ ህጻናትና እናቶች በምግብና ስነ-ምግብ እጥረት እንዳይጎዱ አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው ብለዋል።

በሲዳማ ክልል ሸበዲኖ ወረዳ የተደረገው የመስክ ምልከታ ግንዛቤ ማሳደግና በየቀበሌው ያለውን ከፍተኛ ሀብት አቀናጅቶ በመጠቀም የህብረተሰቡን ኑሮ መቀየር የሚያስችልና የመረዳዳት እድልን መፍጠር ያለመ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት መረዳት፣ በየአካባቢው ያሉ ልምዶችን መፈተሽ፣ ልምዶቹን ማደራጀትና ቅርጽ በማስያዝ ለትግበራ አስቻይ የሆነ የፖሊሲ ድጋፍ ተዘጋጅቶ ምላሽ ለመስጠት ይሰራል ብለዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በምክክር መድረኩ ከተገኙ ልምዶችና ከተቀመጡ አቅጣዎጫች ክልሎችም የራሳቸውን ፕሮግራም ነድፈው ለትግበራው በትጋት እየተንቀሳቀሱ ነው።

ሀገር አቀፉ የሌማት ትሩፋት ፕሮግራምና የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በምግብና ስነ ምግብ ስራ ለሚከናወኑ ስራዎች አጋዥ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል ቡሳ ጎኖፋ ሃላፊ አቶ ሞገስ ኢዳኤ በበኩላቸው ተቋሙ በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ለሚያጋጥመው ችግሮች ሀገር በቀል ምላሽ ለመስጠት በተሰራ ስራ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።

23 ሚሊዮን የሚጠጉ አባላትን በማደራጀት በሚያዋጡት ገንዘብ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በራስ አቅም መፍታት መቻሉን ገልጸው በትምህርት ተቋማት የተማሪዎች ምገባን እንደ አብነት አንስተዋል።

በዘንድሮ ዓመት ከህብረተሰቡ በተዋጣ 6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ተማሪዎችን በመመገብ በምግብና ስነ ምግብ እጥረት የሚያጋጥሙ ጉዳቶችን ለመቀነስ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዚህም የሰቆጣን የቃል ኪዳን ስምምነት ተግባራዊ ከማድረግ ባለፈ በሀገር በቀል ሃብት ሰብዓዊ ድጋፍ ማሟላት እንደሚገባ ለሚጠቁመው የኮሚሽኑ እቅድ ትልቅ አበርከቶ እንዳለው ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽር አቶ አበራ ዊላ በበኩላቸው የመስክ ምልከታ የተደረገበት የሸበዲኖ ወረዳ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግትና አነስተኛ የማሳ ሽፋን ያለበት ነው ብለዋል።

በኮሚሽኑና በአጋር አካላት ድጋፍ በዶሮና ከብት እርባታ፣ የተሻሻለ የአቮካዶ ችግኝ በማፍላትና በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሰማሩ በማድረግ በኢኮኖሚና በተመጣጠነ ምግብ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በላድርሻ አካላት፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና አጋር ድርጅቶች በተገኙበት መድረክ በቀረቡ ሰነዶችና ተሞክሮዎች ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የመስከ ምልከታም ተደርጓል።

ኢ.ዜ.አ