በዘንድሮ አመት የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተማሪዎች የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ከመደበኛ ማስተማር ስራ ባለፈ ተጨማሪ ማጠናከሪያ በመስጠት ላይ እንደሚገኙ የማሻ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህራን ተናገሩ ::
እየተሰጠ ያለው የማጠናከሪያ ትምህርት ጥሩ ውጤት እንዲመዘገብ ስለሚረዳ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ነው ተፈታኝ ተማሪዎች በበኩላቸው የገለፁት ::
የትምህርት ቤቱ ምክትል ርዕሰ መምህር አቶ ትግሉ ኢሞ እንደገለፁት የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል በትምህርት ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ከመምህራን እና ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር በመግባባት ወደ ተግባር እንደተገባ ገልጸው በዚህ መነሻ ለተማሪዎች ከመደበኛ ክፍለ ጊዜ በተጨማሪ ማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
አክለውም ለዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ተፈታኝ ተማሪዎች ከትምህርት ክፍለ ጊዜ ውጭ ተማሪዎች በመረጧቸው መምህራን ከሰኞ እስከ አርብ ለሁለት ሰዓት ማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረው የማሻ ከተማ አስተዳደር ከሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ጋር በመነጋገር ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ቅዳሜና እሁድ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
አምና በተመሳሳይ ወቅት ከ9ኛ እስከ 11ኛ ክፍል 37.7 % ከነበረው የመጠነ ማለፍ ምጣኔ ወደ 68.2 % ማሳደግ እንደተቻለም አቶ ትግሉ ገልፀዋል::
ካነጋገርናቸው የማጠናከሪያ ትምህርት እየተከታተሉ ከሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል ተማሪ ተማመን መሸሻና ተማሪ ሳምራዊት ገዛሄኝ እንደገለፁት ለፈተና እንዲዘጋጁ ትምህርት ቤቱ የተሻለ ድጋፍ እያደረገላቸው ቢሆንም የመማሪያ መጻሕፍት እጥረትና የቤተ-ሙከራ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል።
ተማሪዎቹ አያይዘው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተመዘገበው ያለውን ዝቅተኛ የተማሪዎች ውጤት በማየት ሌሎች ተማሪዎችተስፋ እንዳይቆርጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል::
የማሻ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ አቾሞ በበኩላቸው ባለፈው ዓመት ከከተማው 6 ተማሪዎች ብቻ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ማለፍ መቻላቸውን ተናግረው በዘንድሮው ተማሪዎች በክልላዊና በሀገራዊ ፈተናዎች ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንዲችሉ ጽህፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ዘጋቢ :- ልጃለም ማሞ
More Stories
የ12ኛ ክፍል ፈተና ምዝገባ ከነገ በስቲያ ያበቃል
በትራንስፖርት ዘርፍ የሚስተዋለውን ዘርፈብዙ ችግር ለመቅረፍ የትራንስፖርት ማህበራት ቅንጅትና መናበብ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ
የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ የሥራ አመራር ቦርድ 1ኛ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አስተላልፏል።