January 22, 2025

Masha Fm Woreda to World

Woreda to World

የመስቀል በዓል በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው

የመስቀል በዓል በመላው ኢትዮጵያ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ነው፡፡

በትናንትናው ዕለት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የደመራ ሥነ – ሥርዓት በደመቀ መልኩ በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ መሠረት ተከናውኗል፡፡

በዛሬው ዕለት ደግሞ የመስቀል በዓል በመላው ኢትዮጵያ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ እየተከበረ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመስቀልና ደመራ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት÷ ደመራ እውነተኛው መስቀል የተገኘበት ጠቋሚ ኮምፓስ ነው፤ ለሀገራችን እድገትና ብልጽግና በአንድነት የመቆም ምሳሌያችን ነው፤ ደመራ አቅጣጫ ነው፤ እውነተኛው መስቀል የተለየበት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያም ልጆቿ የሚቆሙበትና የሚሄዱበት እውነተኛ አቅጣጫ ለተስፋዋ ብርሃን፣ ለጥንካሬዋም ፈለግ ይሆናታልም ነው ያሉት፡፡

ልክ መስቀሉን ፈልጎ ማግኘት እጅግ ከባድ ሆኖ ጊዜ እንደወሰደው ብልጽግናን መሻትም እንዲሁ ብዙ ድካምና ጥረት ይፈልጋል ያሉ ሲሆን÷ መስቀሉን ማግኘት የብዙዎችን መተባበርና ምክር እንደመፈለጉ በሀገራችን ብልጽግናን ማረጋገጥም በዚሁ ልክ መተባበርና አብሮነትን መፈለጉ ከልቦናችን ይቀመጥ ሲሉ ገልፀዋል፡፡

በበዓሉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተወካያቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብረሃም በኩል መስቀል ድህነትን የሚሰጥ እንዲሁም ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነት የሚሰበክበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ምዕመናን የመስቀሉን አስተምህሮ በመከተል የፍቅር ምሳሌ የሆነውን በዓል በአብሮነትና በጋራ ማክበር ይገባል ነው ያሉት ብፁዕነታቸው።

የመስቀሉ ምልክት በሆኑት ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት፣ አንድነትና ይቅርታ መኖር እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።